ከኡስታዝ አህመድ ዲን ጀበል ጠቃሚ አስተምህሮ የተወሰደ
“ክርስቲያኖች ተሰደው ሲመጡ ተቀበልናቸው”
በአሕመዲን ጀበል
እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ነበርን።ከመካከለኛ ምስራቅ በቅድሚያ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ተሰደው ወደኛ ሲመጡ በእንግድነት ተቀበልናቸው።እነርሱም እምነቱን መስበክ ጀመሩ። ከኛ ዉስጥ ጥቂቶች እምነቱን ተቀበሉ።
ቀጥሎም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ330 ፍሪምናጦስ በተባለ ወጣት መሪነት ጥቂት የሶሪያ ክርስቲያኖች በስደት ወደ አክሱም መጡ። በእንግድነት ተቀበልናቸው። እምነታቸውን እንዲሰብኩ ፈቀድንላቸው።ክርስትናን መስበክ ጀመሩ። የአክሱሙ ንጉሥ ኢዛናን ጨምሮ ከኛ ዉስጥ ጥቂቶች ክርስትናን ተቀበሉ። ወጣት ፍሪምናጦስ ጳጳስ ፍለጋ ወደ ግብጽ አመራ።
ንጉሡ ኢዛና ክርስትናን እንዲቀበል እንዳደረገ ገለጸ። ንጉሡን ክርስትና ማስነሳት ከቻልክ አንተኑ ጳጳስ እናድርግህ ብለው “አባ ሰላማ” ብለው ቀቡት። ክርስትናን የተቀበሉት ኢትዮጵያውያን ደግሞ “ከሳቴ ብርሃን” ብለው ሰየሙት።
ክርስትና ከ330 እስከ 451 ድረስ የአክሱም ቤተ መንግስት ሃይማኖት እንጂ የአጠቃላዩ ሕዝብ ሃይማኖት መሆን አልቻለም ነበር።
በአምስተኛው ክፍለ ዘመን በሰሜን ኢትዮጵያ ክርስትናን ለሕዝቡ የሰበኩትና ‹‹ዘጠኙ ቅዱሳን›› በሚል የሚታወቁት የሃይማኖት አባቶች ሁሉም መጤና የመካከለኛ ምስራቅ ስደተኞች ናቸው።
እነዚህ ስደተኞች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተሰደው የመጡት እ.ኤ.አ በ451 ከተካሄደው ‹‹ቻልኬዶን ጉባዔ›› በኋላ ነበር። ስደተኞቹ የሃይማኖት አባቶች አባ አፍጼ፣ አባ አሌፍ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጉባ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ጴንጤሌዎን፣ አባ ጻሕማ፣ አባ የማታ፣ እና አባ ዘሚካኤል ዓረጋዊ ናቸው።
(The Dictionary of Ethiopian Biography, Vol.1, From Early times to the End of the Zagwe Dynasty C.1270 AD, Institute of Ethiopian studies, Addis Ababa University, 1975, Pp. 209-210)
ቀጥሎም በ615 ከመካ የኢስላም እምነት ተከታይ ሰሀቦች ተሰደው መጡ። ነጻነት በመስጠት የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በመቀበል በሀገራችን እንዲኖሩ ፈቀድንላቸው። እምነቱን ሰበኩ።
ከኛ ዉስጥም ጥቂቶችም ኢስላምን እንደ እምነት ተቀብለው ሙስሊም ሆኑ። በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ጥቂት ስደተኞች በዚሁ ሞተው በትግራይ ተቀበሩ። የተቀሩት ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ክርስትና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ330 ወደ አክሱም ሲገባ ኢስላም ደግሞ ክርስትና ወደ አክሱም ከገባ ከ285(ከሁለት መቶ ሰማንያ አምስት) ዓመታት በኋላ ማለት በ615 ነበር የገባው።
ከዚያ በኋላ እኛ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ጊዜ በተቀበልናቸው ሃይማኖቶች ምክንያት እምነታችን የተለያየ ሆነ። ከፊሉ አይሁድ፥ ከፊሉ ክርስቲያን፥ ከፊሉ ሙስሊም ሆነ።
ቀጥሎም በ16ኛ ክፈለ ዘመን ካቶሊኮች ወደ ሀገራችን ተሰደው መጡ።ተቀበልናቸው። እምነታቸውን መስበክ ጀመሩ። ከኛ መካከል ከፊሎች የካቶሊክ እምነትን ተቀበሉ።
ቀጥሎም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ መጡ።ተቀበልናቸው።እምነታቸውን እንዲሰብኩ እኛ ኢትዮጵያውያን ፈቀድንላቸው። በዚህ ሁኔታ እኛ ኢትዮጵያውያን እምነታችንን እየቀያየርን ቀጠልን። ከፊላችን ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ወዘተ እየሆንን ቀጠልን።
ከላይ በተጠቀሰው መልኩ በመጤ ስደተኞች የተሰበከውን እምነት እየተከተልን ዘለቅን።ነገር ከኛ መካከል በመጤ ስደተኞች የተሰበከው የአንዱ እምነት ከፊል ሰባኪዎች “ሌሎች እንጂ እኛ መጤ አይደለንም።” የሚል እይታ ያዙ።በእርግጥ መጤዎቹ እምነቱን ያመጡልን እንጂ እኛ የተቀበልነው ኢትዮጵያውያን አይደለንም።
ከእምነቶቹ መምጣት በፊት ሀገርና ህዝብ ነበር።ዛሬም ሀገራችን የሁላችንም ስለሆነች ሁላችንን በምትመስልና እኩል በምትወክል መልኩ እንገንባት የሚል ጥያቄ ሲነሳ “እኛ ነባር እናንተ መጤ” የሚል የድንቁርና ጫወታ መጫወት ያማራቸውን ታዘብን።
እኔም ሀገራችን የሁላችንም ናትና መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዲስተካከል ሀሳብ ሳነሳ አፍ በማዘጋት ዝም ለማሰኘት ጥቂቶች ተረባረቡ። አክራሪ፣አይ፣ ኤስ፣ወሃቢያ፣ የእጌሌ ተላላኪ፣ ኢስላማዊ መንግስት ሊመሰርቱ አቅደዋል፣ሌላም ሌላም።
ያሻችውን ይበሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተሰደው ሲመጡ በመቀበላችን እንደምንኮራው ክርስቲያን ስደተኞችን በመቀበላችን እንኮራከን።
ቸር እንሰንብት!